Main Article Content

የራስመር መማር ብልሃቶች (Self-regulated learning strategies) በማንበብ ተነሳሽነትና በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ያላቸው ሚና፤ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ተተኳሪነት


ታደሰ ዳርገው
ማረው አለሙ
Mulugeta Teka

Abstract

የጥናቱ ዋና ዓላማ የራስመር መማር ብልሃቶች አንብቦ የመረዳት ችሎታንና የማንበብን ተነሳሽነት የማሳደግ ሚና መመርመር ነው፡፡ ዓላማውን ለማሳካትም ፍትነትመሰል የጥናት ንድፍ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ በጎንደር ከተማ አስተዳደር በልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤት በ2010 ዓ.ም ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ በትምህርትቤቱ ከሚገኙ የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በአንድ መምህር ከሚማሩ አምስት ክፍሎች ተማሪዎች ውስጥ 74 እና 75 ክፍሎች በተራ የእጣ ናሙና ዘዴ ተለይተዋል፡፡ መረጃዎቹ በቅድመትምህርትና በድኅረትምህርት በአንብቦ መረዳት ፈተናና በማንበብ ተነሳሽነት የጽሑፍ መጠይቅ ተሰብስበዋል፡፡ በአንብቦ መረዳት ፈተናውና በማንበብ ተነሳሽነት የጽሑፍ መጠይቁ የተሰበሰቡት መረጃዎች በየአይነታቸው ከተደራጁ በኋላ በአማካይ ውጤት፣ በልይይት ትንተናና በአበር ልይይት ትንተና ተሰልተው ተተንትነዋል፡፡ በቅድመትምህርት በአንብቦ የመረዳት ፈተናና በማንበብ ተነሳሽነት የጽሑፍ መጠይቅ ተመጣጣኝ አማካይ ውጤቶች የተመዘገበባቸው የሙከራውና የቁጥጥሩ ቡድኖች በድኅረትምህርት ፈተናና በድኅረትምህርት የማንበብ ተነሳሽነት የሙከራው ቡድን ተማሪዎች ከቁጥጥሩ ቡድን ተማሪዎች የበለጠ ጉልህ የሆነ ልዩነት (P= <0.05) አሳይተዋል፡፡ ይህ ውጤትም የራስመር መማር ብልሃቶች የተማሪዎችን የአንብቦ መረዳት ችሎታና የማንበብን ተነሳሽነት ከማሻሻል አኳያ ጉልህ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል አመላክቷል፡፡


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919