Main Article Content

የራስመር መማር ብልሃቶች (Self-regulated learning strategies) አንብቦ የመረዳት ችሎታንና ብልሃቶች አጠቃቀምን የማሳደግ ሚና፤ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ተተኳሪነት


ታደሰ ዳርገው
ማረው አለሙ
ሙሉጌታ ተካ

Abstract

የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ የራስመር መማር ብልሃቶች አንብቦ የመረዳት ችሎታንና የብልሃቶችን አጠቃቀም የማሳደግ ሚና መመርመር ነው፡፡ ዓላማውን ለማሳካትም ፍትነትመሰል የጥናት ንድፍ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ በጎንደር ከተማ አስተዳደር በልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤት በ2010 ዓ.ም ትምህርታቸውን የተከታተሉ የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ በትምህርትቤቱ ከሚገኙ የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በአንድ መምህር ከሚማሩ አምስት ክፍሎች ተማሪዎች ውስጥ ሁለቱ ክፍሎች በተራ የእጣ ንሞና ዘዴ ተለይተዋል፡፡ መረጃዎቹ በአንብቦ መረዳት ፈተናና በብልሃቶች አጠቃቀም የጽሑፍ መጠይቅ በቅድመትምህርትና በድኅረትምህርት ተሰብስበዋል፡፡ መረጃዎቹም በየአይነታቸው ከተደራጁ በኋላ በአማካይ ውጤትና በልይይት ትንተና (ANOVA) ተሰልተው ተተንትነዋል፡፡ የተገኙት ውጤቶች እንደሚያሳዩት በድኅረትምህርት ፈተናና በድኅረትምህርት የብልሃቶች አጠቃቀም፤ የሙከራው ቡድን ተማሪዎች ከቁጥጥሩ ቡድን ተማሪዎች በስታትስቲክስ ጉልህ ልዩነት (P = <0.05) አሳይተዋል፡፡ ይህ ውጤትም የራስመር መማር ብልሃቶች የተማሪዎችን የአንብቦ መረዳት ችሎታና የብልሃቶችን አጠቃቀም ከማሻሻል አኳያ ጉልህ ሚና እንዳለው አመላክቷል፡፡


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919