Main Article Content

በአማርኛ ቋንቋ አንብቦ የመረዳት ችሎታና የራስመር መማር ብልሃቶች አጠቃቀም ተዛምዶ፤ በአስራአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ተተኳሪነት


ይድነቃቸው ገረመው
ገረመው ለሙ
ሰይድ ይመር

Abstract

የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በአማርኛ ቋንቋ አንብቦ የመረዳት ችሎታና የራስመር መማር ብልሃቶች አጠቃቀም መካከል ያለውን ተዛምዶ መፈተሽ ሲሆን፤ ጥናቱ በተላውጦዎች መካከል ያለን ግንኙነት የሚፈትሽ በመሆኑ ተዛምዷዊ የምርምር ንድፍን ተከትሏል፡፡ እኩል እድል ሰጭ በሆነው ተራ የእጣ ንሞና ዘዴ በመጠቀም የተመረጡት የጥናቱ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁለት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤቶች የሚማሩ የአማርኛ ቋንቋ አፍፈት የሆኑ ሁለትመቶ ሶስት የአስራአንደኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የጥናቱ ተሳታፊዎች መረጃ ለመሰብሰብ የአንብቦ መረዳት ችሎታ መለኪያ ፈተናና የራስመር መማር ብልሃቶች አጠቃቀም የጽሁፍ መጠይቅ በጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በመረጃ ትንተናው ገላጭና ተንባይ ስታቲስቲካዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ተከናውኗል፡፡ የአማካዮች፣ የመደበኛ ልይይቶች እና የፒርሰን ፕሮዳክት ሞመንት ኮሪሌሽን ትንተና ተደርጓል፡፡ ከመረጃ ትንተናዎቹ በተገኙት ውጤቶች መሰረትም የአስራአንደኛ ክፍል አማርኛ ቋንቋ አፍፈት ተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታ በምን ደረጃ ላይ እንደሆነ ለሚጠይቀው የጥናቱ ጥያቄ የፈተናው አማካይ ውጤትና የውጤት ስርጭቱ አብዛኞቹ ተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታቸው መካከለኛ ሲሆን፤ የጥናቱ ተሳታፊ ተማሪዎች የራስመር መማር ብልሃቶች አጠቃቀም ምን ደረጃ ላይ እንደሆነ ለማወቅ በተደረገ የአማካዮች ፍተሻ ደግሞ፤ በንዑስ ዘርፎች ደረጃና በአጠቃላይ መጠይቅ ደረጃ የተገኘው ውጤት እንዳሳየው የተማሪዎቹ የራስመር መማር ብልሃቶች አጠቃቀም መካከለኛ ነው፡፡ በመጨረሻም በተሰራው የፒርሰን ተዛምዶ ትንተና ውጤት መሰረት በአስራ አንደኛ ክፍል አማርኛ ቋንቋ አፍፈት ተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታና የራስመር መማር ብልሃቶች አጠቃቀም መካከል ጉልህ ተዛምዶ አልታየም፡፡


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919