Main Article Content

ጽንሰ ሐሳብ ተኮር የማንበብ ትምህርት፣ በማንበብ ታታሪነትና በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ያለው ተጽዕኖ፤ በአካባቢ ሣይንሥ ትምህርት፣በአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ተተኳሪነት


አፀደ ማሩ
ማረው አለሙ
ብዙአየሁ ቀሪሰው

Abstract

የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ አካባቢ ሣይንሥን በጽንሰሐሳብተኮር የማንበብ ትምህርት መማር በማንበብ ታታሪነትና በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ ያለውን ተጽዕኖ መፈተሽ ነበር፡፡ ጥናቱ ቅደመትምህርትና ድኅረትምህርት ባለቁጥጥር ቡድን ፍትነትመሰል (quasi experiment) ስልት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች በባሕር ዳር ከተማ በዕውቀት ፋና አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤት በ2014 ዓ.ም ከነበሩ ዐራት የዐምስተኛ ክፍል መማሪያ ክፍሎች ውስጥ በቀላል የዕጣ ንሞና ዘዴ የተመረጡ የኹለት ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ በዚህም በቁጥጥር ቡድኑ 48 እና በፍትነት ቡድኑ 48 በድምሩ 96 ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ የፍትነት ቡድኑ ለዐምስት ሳምንታት (ለ20 ክፍለጊዜያት) በጽንሰሐሳብተኮር የማንበብ ትምህርት (በማንበብ የግንዛቤ ብልሃቶችና የተነሳሽነት የድጋፍ ተግባራት)፣የቁጥጥር ቡድኑ በመደበኛው ሥርዓተትምህርት ስልት አካባቢ ሣይንሥን ተምረዋል፡፡ የጥናቱ መረጃዎች በአንብቦ መረዳት ፈተናዎችና በማንበብ ታታሪነት መጠይቅ በቅድመትምህርትና በድኅረትምህርት ተሰብስበዋል፡፡ የመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎቹ ተገቢነት በፍተሻዊና በአረጋጋጭ የፋክተር ትንተና ስልቶች (Exploratory & confirmatory factor analysis) እና አስተማማኝነቱ በውስጣዊ ወጥነትና (internal consistancy) በተቀናጀ አስተማማኝነት (composit reliability) ተረጋግጧል፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች የጾታ ተመጣጣኝነት በካይ ካሬ፣ የዕድሜና የዳራዊ ዕውቀት አቻነት በባዕድ ናሙና ቲ-ቴስት ተለክቷል፡፡ የጥናቱ መረጃዎችም በSPSS AMOS 23 ሶፍትዌር በመታገዝ በመዋቅራዊ ስሌት ሞዴል ስልት (Structural equation model) ተተንትነዋል፡፡ በዚህም ጽንሰሐሳብተኮር የማንበብ ትምህርት በተማሪዎች አንብቦ የመረዳት ችሎታ (β=.34, t= 2.8, p<0.05) እና በማንበብ ታታሪነት (β=.65, t= .4.76, p<0.05) ላይ ቀጥተኛ፣ የማንበብ ታታሪነትን በማጎልበት በአንብቦ መረዳት ችሎታ ላይ (B=.18, t=1.3, p<0.05) ኢቀጥተኛ ተጽዕኖ እንዳለው የውጤት ትንተናው አመላክቷል፡፡ በዚህም መሰረት በጽንሰሐሳብተኮር የማንበብ ትምህርት አተገባበር ላይ የመፍትሔ ሐሳቦች ተጠቁመዋል፡፡


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919