Main Article Content

የጌጦች አሠራርና ፋይዳ በአርጎባ ብሄረሰብ


አብዩ አስማማው

Abstract

ይህ ጥናት “የማጌጫ ቁሶች አሠራርና ፋይዳ በአርጎባ ብሄረሰብ” በሚል ርዕስ ሲዘጋጅ የብሄረሰቡን የማጌጫ ቁሶች የመለየትን፣ በናሙና ቁሶች ላይ በማተኮር ቁሶችን ከቁስነታቸው አልፎም ከባህል መገለጫነታቸው አንፃር ትንታኔ የማቅረብን፣ ወዲያውም በቁሶችና በባለቤት ብሄረሰቡ መካከል ያለን ግንኙነት አጉልቶ የማሳየትን ዓላማ ይዞ የተነሳ ነበር። እነዚህንም ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ፣ አጥኝው፣ የቃል መጠይቅንና ምልከታን በመረጃ መሰብሰቢያነት ተገልግሏል። በተጠቀሱት የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች የተገኙት መረጃዎችም ከSchelereth ቁሳዊ ባህልን የመተንተኛ ሞዴሎች አንፃር የተተነተኑ ሲሆን የትንታኔው ውጤትም የሚከተለው ነው። በናሙናነት የተመረጡትና ለትንታኔ የቀረቡት “6” (ስድስት) ቁሶች ናቸው። እነዚህም ቁሶች ብሄረሰቡ በአካባቢው በቀላሉ ከሚያገኛቸው ንጥረ ቁሶች (ከብር፣ ከነሃስ፣ ከኒኬልና ከሸማ) የተሠሩ ሆነው ተገኝተዋል። ከሚውሉበት የሰውነት ክፍል አንፃርም፣ የአንገት፣ የእጅ፣ የወገብና የእግር ተብለው ተመድበዋል። በጥናቱ የተተነተኑት ቁሶች በብሄረሰቡ አባላት ዘንድ አገልግሎት ላይ በሚውሉበት ጊዜ፣ ቀድሞ ከተሠሩለት ዓላማ ባሻገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃን የሚያመላክቱ፣ የእርስ በርስ መስተጋብርን የሚያሳዩ ናቸው። ከዚህም ባሻገር፣ ከSchelereth የ“አገልግሎት ሰጭነት”፣ “መዋቅራዊነት”፣ “ባህርይ አመላካችነት”፣ “ተምሣሌታዊነት”፣ “ማህበራዊነት”፣ “ጥበብን አመላካችነት” እና “ማህበረሰብ ጠቃሽነት” ሞዴሎች አንፃር የሚተነተኑ፣ ወዲያውም ሞዴሎችን ለማብራራት በአስረጅነት የሚቀርቡ ሆነው ተገኝተዋል። ከላይ የተጠቀሱትን የጥናቱን ግኝቶችና የተጠኝ አካባቢውን ነባራዊ ሁኔታዎች መነሻ በማድረግም፣ አጥኝው፣ የልዩ ወረዳው የባህልና የማስታወቂያ ጽ/ቤቶች የብሄረሰቡን ቁሶች በመለየቱና በመሠነዱ፣ የእጅ ባለሙያዎችንም በመደገፉ ረገድ ሥራዎችን ቢሠሩ የሚሉ የይሁንታ ሃሳቦችን ሠንዝሯል። ከዚህም ባሻገር፣ የቁሳዊ ባህል ጉዳይ የሚመለከታቸው ተቋማት የውይይትና የምርምር መርኃ ግብሮችን ቢቀርፁና መስኩን ቢያበለፅጉት የሚል ተጨማሪ ሃሳብ አቅርቧል።


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919