Main Article Content

የ‹ሙዳ› ስርዓተከበራ ክወና እና ትዕምርታዊ ውክልና፤ በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነቅርስ


ሰሎሞን ተሾመ

Abstract

የዚህ ጥናት አቢይ ዓላማ በድሬ ሼኽ ሁሴን መካነቅርስ የሙዳ ስርዓተከበራ የአከዋወን ቅደምተከተልና ክወናው ያለውን ትዕምርታዊ ውክልና መተንተን ነው፡፡ የድሬ ሼኽ ሁሴን መካነቅርስ በባሌ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ፣ አናጂና ቀበሌ የሚገኝና በአስራ ሁለተኛው መቶ ክፍለዘመን እንደተመሰረተ የሚነገር ኃይማኖታዊ ስፍራ ነው፡፡ የሙዳ በዓላት በመካነቅርሱ በአመት ሁለት ጊዜ የሚከበሩ የመታሰቢያ ስርዓተከበራዎች ናቸው፡፡ ጥናቱ ይዘታዊ ምርምር የጥናት አይነትን የተከተለ ነው፡፡ ለጥናቱም ምልከታና ቃለመጠይቅ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ የተሰበሰቡ መረጃዎች ያላቸውን ትርጉም በፍከራ ለማሳየት የክወና እና ትዕምርታዊ ንድፈሃሳቦችን መሰረት በማድረግ የተዘጋጀ ጥናት ነው፡፡ በሙዳ በዓል ወቅት የሚከወኑ ስርዓተከበራዎች በዋሬ ስፍራ፣ በከራ ጉዶ እና በቅጽር ግቢው ውስጥ እንዲሁም በአይናገኜ ገደል የሚከወኑ እንደሆኑ ጥናቱ ያሳያል፡፡ በሙዳ በዓላት ወቅት የሚከወኑ ስርዓተከበራዎች ለመንፈሳዊ ተጓዦች መንፈሳዊ እሴትን፣ የመንፈስ ለውጥን፣ የምሉዕነት ስሜትንና እርካታን የሚያጎናጽፉ እንደሆኑ ጥናቱ ያሳያል፡፡ የሙዳ ስርዓተከበራዎች ከማህበራዊና ሀይማኖታዊ ዋጋ አንጻር ልዩ ስፍራ የሚሰጣቸው ክወናዎች እንደሆኑ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ስርዓተከበራዎቹም በቅደምተከተላዊ ስርዓት፣ በተደጋጋሚና በመደበኛነት የሚከወኑ ጠቃሚ ድርጊቶችና ሕዝባዊ ሁነቶች ናቸው፡፡ የሙዳ ስርዓተከበራዎች የመንፈሳዊ ተጓዦችን፣ የአማኞችንና የከዋኞችን መንፈሳዊ፣ አዕምሯዊና ማህበራዊ ደረጃን ከፍ በማድረግ ከመንፈሳዊ ሀይሎች ጋር ግንኙነት ለመመስረት እንደሚረዳ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ስርዓተከበራዎቹ የማህበረሰቡን ማንነት ለመፍጠር፣ ለመጠበቅ፣ እውቅና ለመስጠት ዋና መሰረት እንደሆኑ እንዲሁም የእርስበርስ ተግባቦት የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጥናቱ አሳይቷል፡፡


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919