Main Article Content

ተከታታይ የሙያ ማበልፀጊያ የአማርኛ ቋንቋ መምህራንን የማስተማሪያ ዘዴና አመለካከት ለመለወጥ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ፍተሻ


ሙሉጌታ ይታየው ደርሰህ

Abstract

የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ ተከታታይ የሙያ ማበልፀጊያ ስልጠና ለአማርኛ ቋንቋ መምህራን የማስተማሪያ ዘዴና አመለካከት መጎልበት ያበረከተውን አስተዋጽኦ መፈተሽ ነው። ከምርምሩ ዓላማና ከምርምሩ ጥያቄዎች በመነሳት በዚህ ጥናት ውህዳዊ የምርምር ዓይነት ተግባር ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ አካሄዱም የገላጭ ዘዴን መሰረት ያደረገ ነው። የጥናቱ ተሳታፊዎች በምስራቅ ጎጃም ዞን ከሚገኙ 20 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በጉድኝት የናሙና መምረጫ ዘዴ የተመረጡ 11 ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ፣ ተጠኝዎችም በዞኑ ከሚያስተምሩ 156 የአማርኛ ቋንቋ መምህራን ውስጥ በዓላማ ተኮር የንሞና ስልት የተመረጡ 52 መምህራን ናቸው። የጥናቱ መረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎችም የክፍል ውስጥ ምልከታ፣ ቃለመጠይቅ፣ የተተኳሪ ቡድን ውይይትና የጽሑፍ መጠይቅ ሲሆኑ፣ ሁሉም የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች በባለሙያ ተፈትሸውና ተገምግመው ማስተካከያ ከተደረገባቸው በኋላ ቅድመ ጥናት ሙከራ ተደርጎባቸው ሥራ ላይ ውለዋል። የጽሑፍ መጠይቁን በተመለከተ  የሙከራ ጥናቱ መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ በክሮንባች አልፋ ቀመር ተሰልቶ 0.948 ውጤት በመገኘቱ ትክክለኝነቱና አስተማማኝነቱ ተረጋግጦ በስራ ላይ ውሏል። ከላይ በተጠቀሱት የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች የተሰበሰቡት መረጃዎችም ዓይነታዊው፣ በጭብጥ በጭብጥ ተደራጅቶ ሲተነተን፣ መጠናዊው ደግሞ በመቶኛ እየተሰላ ተተንትኗል። ትንተናው የተከናወነው ዓይነታዊው እየቀደመ መጠናዊው እየተከተለ ሲሆን፣ ይህም ዓይነታዊ-መጠናዊ አቀራረብን (QUAL-Quan model) የተከተለ ነው። ይህ አቀራረብ የዓይነታዊ ምርምር ተግባራትን የሚያስቀድም ከመሆኑም በላይ በዓይነታዊ ምርምር የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች ለተሰበሰቡ መረጃዎች ክብደት የሚሰጥ ነው። በውጤቱም ተከታታይ የሙያ ማበልፀጊያ  ስልጠና የአማርኛ ቋንቋ መምህራንን የማስተማር ዘዴና አመለካከት በመለወጥ ረገድ ያበረከተው አስተዋጽኦ  ውሱን መሆኑ ተመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ  መምህራኑ ከስልጠና በኋላም ሆነ በስልጠና ወቅት የሚያገኙት ማበረታቻ ባለመኖሩ ለስልጠናው ያላቸው ፍላጎትም ዝቅተኛ እንደሆነ የጥናቱ ውጤት ይጠቁማል። ስልጠናው ከላይ ወደታች የሚጫን፣ የመምህራኑን ጊዜ፣ ጉልበትና ፍላጎት ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ውጤታማ አለመሆኑ በቃለመጠይቁና በተተኳሪ ቡድን ውይይት ወቅት ጎልቶ ተስተውሏል። ስለዚህ፣ የስልጠናው አተገባበርና ይዘት ከመምህራን ከራሳቸው እንዲመነጭ ቢደረግና የመምህራን ተሳትፎ ቢታከልበት የሚሻል ይሆናል።


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919