Main Article Content

በኢትዮጵያ አጠቃላይ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የዐማርኛ ቋንቋ ፈተና የቅደምተከተል (sequencing) አስተካክል ጥያቄ ግምገማ


ማረው ዓለሙ

Abstract

የዚህ ጥናት ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ኹለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ የዐማርኛ ቋንቋ ትምህርት ፈተና የቅደምተከተል አስተካክል ጥያቄዎችን መገምገም ነው፡፡ የጥናቱ የመረጃ ምንጭች ከ1998-2004 ዓ.ም. የሰባት ዓመት የዐማርኛ ቋንቋ ፈተና ጥራዞች ናቸው፡፡ በኹሉም ጥራዞች የተገኙት ስምንት የቅደምተከተል አስተካክል ናሙና ጥያቄዎች የጥናቱ መረጃዎች ናቸው፡፡ ጥናቱ የተከናወነው በግምገማ ስልት ሲሆን፣ የግምገማ ትኩረቶችም በቅደምተከተል አስተካክል ጥያቄና በሚለካው የቋንቋ ችሎታ፣ በቅደምተከተል አስተካክል ጥያቄና በሚያስገኘው ነጥብ መካከል ያለው መጣጣም፣ የመነሻ መልስና ለከፊል መልስ ከፊል ውጤት፣ የቅደምተከተል አመላካች አካላትና የጥያቄዎች ነፃነት ናቸው፡፡ የመተንተኛ አሐዱም የዓረፍተነገሮች ቅደምተከተል ነው፡፡ እንዲሁም በሙያው የሚሠሩ ሦስት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ለጥያቄዎቹ በየግላቸው ያዘጋጇቸው መልሶች ለግምገማው በግብዓትነት አገልግለዋል፡፡ በውጤት ትንተናው መሠረትም በቅደምተከተል አስተካክል ጥያቄና በሚለካው የቋንቋ ችሎታ መካከል መጣጣም አልታየም፤ ቅደምተከተል አስተካክል ጥያቄ እንዲለካ የሚጠበቀው የማንበብ ክሂል ችሎታን ቢሆንም፣ በዚህ ጥናት የመረጃ ምንጮች ግን ጥያቄው የቀረበው የመጻፍ ክሂል ችሎታን እንዲለካ ታስቦ መሆኑን ከውጤት ትንተናው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለዚህም ሲባል በአንድ ቅደምተከተል አስተካከል ጥያቄ መሠረት መረጃው ከሚችለው በላይ በቀረቡት ጥያቄዎች መካከል መደጋገፍ ወይም የመረጃ ተጋቦት ታይቷል፡፡ ይህም የጥያቄዎችን ራስን ችሎ አንድን የቋንቋ ችሎታ ዘርፍ የመለካት ብቃት እንደጎዳው የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡ የውጤት ትንተናው እንዳመላከተው ኹሉም የጥናቱ ናሙና ጥያቄዎች በመልስ አስመራጭ ቅርፅ የቀረቡ ኾነው፣ ቢያንስ አንድ መነሻ መልስ ግን የላቸውም፡፡ ይህም በዓረፍተነገሮቹ ከተገቢ የቅደምተከተል አመላካቾች ጉድለት ጋራ ተዳምሮ ጥያቄዎቹን አወሳስቧቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅደምተከተል አስተካክል ጥያቄ የሚጠበቀው መሉ መልስ በመኾኑ በዚህ ረገድ የነጥብ አሰጣጡ የፍትሐዊነት ችግር እንዳለበት የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡ በጥናቱ ውጤት መሠረትም ከቅደምተከተል አስተካክል ጥያቄ ጋራ በተያያዘ የሚከሰቱትን ችግሮች በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ እንዲቻል መፍተሄዎች ተጠቁመዋል፡፡   


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919