Main Article Content

በባህል ሕክምና ዕውቀት የሕመም መንስኤ እሳቤና መለከፊያ ዐዉዶች ትንተና በደቡብ ጎንደር ዞን ማኅበረሰብ


Anteneh Aweke

Abstract

ይህ ጥናት “በባህል ሕክምና ዕውቀት የሕመም መንስኤ እሳቤና መለከፊያ ዐውዶች ትንተና  በደቡብ ጎንደር ዞን ማኅበረሰብ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፣ የጥናቱ ዐቢይ አላማ በባህል ሕክምና ዕውቀት የሕመም መንስኤ እሳቤና መለከፊያ ዐውዶችን መመርመር ነው። ጥናቱ፣ የሕመም መንስኤ እሳቤና መለከፊያ ዐውዶችን መግለጽ፤ በባህል ሕክምና  ሂደት አዎንታዊና አሉታዊ ተግባራትን መጠቆም የሚሉ ዝርዝር ዓላማዎችን አካቷል። እነዚህን ዝርዝር ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ የመስክ መረጃዎች፤ በቃለመጠይቅ፣ በምልከታ፣ በቡድን ተኮር ውይይት እና በንጥል ጥናት ዘዴዎች ተሰብስበው፤ በማስታወሻ፣ በመቅረጸ ድምጽ፣ በፎቶና በቪዲዮ ካሜራ ተሰንደዋል። የመስክ መረጃ ሰጪዎች፤ የኦርቶዶክስ እምነት (98% የአካባቢውን/ነዋሪውን ማኅበረሰብ ይመለከታል) ተከታዮችን ብቻ ታላሚ በማድረግ (ከሶስት ወረዳዎች 76 ሰዎች) በዓላማ ተኮር እና በአጋዥ ጠቋሚ ናሙና ስልት ተመርጠዋል። ከዐብይና አጋዥ መረጃ ሰጪዎች የተሰበሰቡ መረጃዎች፤ በይዘትና በምድብ ተደራጅተው፤ ዓይነታዊ የምርምር ይዘትን በመከተል በሥነ ዕውቀት (Epistemology) እና በማኅበራዊ ግንባታ (Social Constructionist theory)፣ ሕዝባዊ የሕመም መንስኤ ንድፈ ሃሳቦችን (Lay theories of illness Causation) መሰረት በማድረግ፤ ከተፈጥሮ ባሕርይ እና ከባህል-ተኮር ማብራሪያ ሞዴሎች አንፃር በመፈተሽ፤ በገላጭ፣ በይዘት ትንተና እና ትርጓሜ (Interpretation) ስልት ተተንትነው ቀርበዋል። በትንታኔው መሰረት በደቡብ ጎንደር ዞን ማኅበረሰብ /በባህል ሐኪሞች/ እሳቤ፤ የሕመም መንስኤዎች ጅን፣ ዛር፣ ቡዳ፣ የመሬት እና የዐየር ጋኔል ተደርገው እንደሚታሰቡ ጥናቱ ይገልፃል። የሕመም መለከፊያ ዐውዶች፤ በሕሊና ተሰውረው፣ በዐየር ተበትነው የሚኖሩ አጋንንት፤ በዕፅዋት የሰፈሩ፣ በእንስሳት የሚበሩ አጋንንት፤ በቆሻሻ የሚኖሩ፣ በወንዝ የሰፈሩ አጋንንት፤ በደም፣ ምግብና መጠጥ የሚነሱ አጋንንት እንደሆኑ ጥናቱ አረጋግጧል። ብዙሃኑ የባህል ሐኪሞች ከእምነት ተቋም የወጡ  እና ለማኅበረሰቡ ቅርብና ተደራሽ መሆናቸው፤ ለሕሙማን ልማዱን በጠበቀ መልኩ ስነልቡናዊ ድጋፍ ማድረጋቸው፤ "በዝቅተኛ ወጪ" እና በውለታ አገልግሎት መስጠታቸው የሕክምና ሂደቱን ተመራጭ ቢያደርገውም፤ ከዘመኑ ሕክምና ልማድ፣ ከሕመም መንስኤ እሳቤና መለከፊያ ዐውዶች ጋር በተገናኘ ጉዳት እንደሚደርስ ጥናቱ ጠቁሟል። ይህን የባህል ሕክምና ዕውቀት ለማዘመን፤ በዘርፉ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ እገዛ ለማድረግ እና የዘመናዊ ሕክምና አጋር እንዲሆን፤ የባህላዊና የዘመናዊ ሕክምና ባለሙያዎች ተቀራርበው ቢወያዩና ቢመካከሩ፣ በጋራ የሚሰሩበትን አጋጣሚ ቢያመቻቹ፤ ቀጣይ ውይይቶችና ጥናቶች ቢካሄዱ የተሻለ መሆኑን በመጠቆም ጥናቱ ተጠናቋል።


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919