Main Article Content

የባህላዊ ስእሎችና ቅርጻቅርጽ የአሰራር ልማድና ፋይዳ በዘጌ ማኅበረሰብ


ሞገስ ሚካኤል

Abstract

ይህ ጥናት ትኩረቱ በጣና ሀይቅ ውስጥ በሚገኘው የዘጌ ባሕረ ሰላጤ ላይ ሆኖ በዋናነትም በባሕረ ሰላጤው በሚኖረው ማኅበረሰብ የሚሰሩ ስእሎችና ቅርጻቅርጽ ላይ ነው፡፡ ዐቢይ ዓላማውም የስእሎችንና የቅርጻቅርጽን የአሰራር ልማድና ተግባራት ማሳየት ነው፡፡ ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በዓላማ ተኮር ናሙና አንድ የከተማ፣ ሶስት የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት፣ ሰባት ገዳማት፣ 18 ቁልፍ፣ 29 ንዑስ መረጃ ሰጪዎች ተመርጠው በአካባቢው ስለሚሰሩ ስእሎችና ቅርጻቅርጽ የአሰራር ልማድ እንዲሁም ተግባር መረጃዎች በምልከታ፣ በቃለመጠይቅና በቡድን ተኮር ውይይት ተሰብስበው በገላጭ ስልት፣ በሥነ ትእምርት (Semiotics) እና በተግባራዊ ንድፈ ሀሳብ (Functionalism) ተተንትነዋል፡፡ በዘጌ ስእል መሳልና ቅርጻቅርጽ መስራት የሃይማኖትና የባህል አካሎች ሲሆኑ ግብዓቶች ሃይማኖታዊ መሰረት ያላቸውና የራሳቸው የሆነ ትእምርት ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ግብዓቶች አብዛኞቹ ከተፈጥሯዊ አካባቢው በቀላሉ የሚገኙና በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ ቀለማትን ማዘጋጀትና ውክልናቸውን በአግባቡ መለየት የሰዓሊው ቀዳሚ ተግባራት ናቸው፡፡ ቀለማት ምንጫቸው ቀስተደመና ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ከቀስተደመና ተቀዱ የሚባሉት ቀለማት አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ፣ ሰማያዊ፣ ጥቁርና ነጭ ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ አራቱ ቀለማት ተፈጥሯዊ ቀለማት/environmental colours/ ናቸው፤ ከአካባቢው የሚገኙ ግብዓቶችን በመጠቀም በባህላዊ እውቀት ተዘጋጅተው መልሰው ተፈጥሯዊ አካባቢን ለመግለጽ የሚውሉ ቀለማት ናቸው፡፡ እነዚህ ቀለማት ቀስተደመና ላይ ጎልተው የሚታዩ በመሆናቸው መለኮታዊ ቀለማት (devine colours) ናቸው፡፡ ቀለማት የራሳቸው ውክልና እና አገልግሎት አላቸው፡፡ ቢጫ ተስፋን፣ ሰማያዊ ሰማያዊ ህይወትን፣ አረንጓዴ ረፍትን፣ ገነትን ወይም ልምላሜን፣ ነጭ ንጹህ ባህርይን፣ ቀይ ሰማእትነትን፣ ጥቁር ክፉ ባህርይን ለመግለጽ ያገለግላሉ፡፡ ቀለማትን ተጠቅመው በሚስሉበት ወቅት ፊት፣ እጅ፣ ዓይን ላይና እነዚህ የሰውነት ክፍሎች ለሚወክሉት ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ስእሎችና ቅርጻቅርጽ ለአስተምህሮት፣ ለጸሎት፣ ለተመስጦና ለፈውስ ተግባር እንደሚውሉ የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡


Journal Identifiers


eISSN: 2518-2919