Main Article Content
ልጅነት በ“ዘላን” እና “አለንጋና ምስር”፤ ሥነ ልቡናዊ ንባብ
Abstract
ይህ ጥናት የአዳም ረታ ስራ ከሆነው “አለንጋና ምስር” የአጫጭር እና ኖቬላ ልቦለዶች መድበል ውስጥ በተመረጡ ሁለት ቴክስቶች (“ዘላን” እና “አለንጋና ምስር”) ላይ የሥነ ልቡና ንድፈ ሃሳቦችን
ምቹ በሆነ ስልት በማልመድ የተደረገ ነው፡፡ በቴክስቶቹ ውስጥ የተቀረጹ ልጅ ገፀ ባህሪያትን ከማኅበረ-ልቡናዊና ‹‹ሳይኮሴክሿል›› ማንነት፣ ‹‹ኤዲፐሳዊ ቅዠት›› (Oedipus complex) እና ‹‹ፍቅዓተ-ኢጎ›› (splitting of the ego)፣ የጨቅላነት ‹‹ግንትሮሽ›› (fixation) እና የሁለት ሰብዕናዎች መቃየጥ አንጻር ለመመርመር ተሞክሯል፡፡ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ሚቶሎጂዎች የተቀዱ መባያዎች ሰብዕናን መርምሮ ለማሳየት ትኩረት ተደርጎባቸዋል፡፡ ጥናቱ ወዲህ በቴክስቶቹ ውስጥ የተቀረጹ ልጅ ገፀ ባህሪያት የብቸኝነት፣ የመከዳትና የመጣል ስሜት የሚስተዋልባቸው እንደሆኑ፣ ወዲህ ደግሞ የአሳዳጊዎቻቸው ሚና አፍራሽ መሆኑ፣ የጨቅላነት ‹‹ሳይኮሴክሿል›› ዕድገት የ‹‹ግንትሮሽ››ና የ‹‹ሣቃዪ ፍለሳ›› (sadistic displacement) ማደሪያዎች እንደሆኑ ተብራርቷል፡፡ ስለሆነም፣
በእነዚህና በትንተናው ውስጥ በ“ተዘነቁ” ሃሳቦች ልጆቹ ማኅበረ-ባህላዊ ኃላፊነትን መሸከም የማይችሉ እንደሆኑ ለማጠቃለል ተሞክሯል፡፡ በመጨረሻም በቴክስቶቹ ውስጥ ልጆቹ የተቀረጹት፣ ማኅበረ-ባህላዊ ስርዓቶችና ተፈጥሯዊ ማንነቶች በመጎራበት ነው ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡